ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት (IPS) ጋር የሁለትዮሽ መግባቢያ ሰነድ (MOU) ተፈራረመ

ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት (IPS) ጋር የሁለትዮሽ መግባቢያ ሰነድ (MOU) ተፈራረመ

ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት (IPS) ጋር የሁለትዮሽ መግባቢያ ሰነድ (MOU) ጥር 13/2017 ዓ/ም ተፈራረመ።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት አዝመራው አየሁ (ዶ/ር) ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተግባር ትምህርት በመስጠትና ችግር ፈቺ ምርምሮችን በመስራት የአካባቢውንና የሀገርን ችግር በመቅረፍ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የማህበረሰብ አገልግሎት የመስጠት ተልእኮዎችን ይዞ ሲሰራ ቢቆይም አሁን ላይ በተሰጠው ሀገራዊ የዩኒቨርሲቲዎች ልየታ መሰረት ወደ አፕላይድ ዩኒቨርሲቲ ጎራ ተመድቦ አፕላይድ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑን ለቡድኑ ገለጻ አድርገዋል። አዝመራው አየሁ (ዶ/ር) ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ሀይል እንድናፈራ፣ ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጓቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንድናመርት፣ ኢንዱስትሪዎችን እንድናማክርና ከኢንዱስትሪዎች ጋር በቅርበት እንድንሰራ የአፕላይድ ዩኒቨርሲቲ አሰራርን ተከትለን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር አዋጅ ወጥቶ ስራ ላይ ውሏል ብለው እኛም ቀድመን የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር አማካሪ ቦርድ አቋቁመን ወደ ስራ የገባን በመሆናችን መደላድል ፈጥረናል ብለዋል። የአማካሪ ድርጅቱ ስራዎች በአብዛኛው ከአፕላይድ ዩኒቨርሲቲ ጋር አብረው የሚሄዱ በመሆናቸውና የካበተ ልምዳችሁን እያካፈለችሁን አብረን በጋራ እንድንሰራ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲን ምርጫችሁ አድርጋችሁ ስለመጣችሁ እናመሰግናለን እንኳን ደህና መጣችሁ ሲሉ ተናግረዋል።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፕሬዚደንት ተወካይና የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ጌትነት አሸናፊ (ዶ/ር) በጋራ ስራ ስንሰራ ውጤታማ መሆን እንደምንችል የሚያስገነዝብ ዩኒቨርሲቲ ለኢንዱስትሪ የሚል ሞቶ ያለው የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ እየፈጠርን መስመራችንን ከኢንዱስትሪው ጋር ማስተካከል ስላለብን ለተመሳሳይ ዓላማና ፍላጎት ነው ዛሬ የተገናኘነው ብለዋል። ዩኒቨርሲቲውና ኢንዱስትሪው በጋራ በቂ ክህሎት ያላቸው ተማሪዎችን እያሰለጠኑ ወደ ገበያው በማቅረብና በመቅጠር ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ያሉ ሲሆን አክለውም የተናጠል የሚባል ስራ አይኖርም ብለዋል። የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች ካሪኩለም በጋራ ከመቅረጽ ጀምሮ መሳተፍና ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ስልጠናዎችን የመስጠትና ሪሶርስ በጋራ የመጠቀም ልምድ ማዳበር ያለባቸው መሆኑን ተናግረው ዩኒቨርሲቲው ብቻውን ወይም ኢንዱስትሪው ብቻውን በተናጠል የሚያመጡት ውጤት እንደሌለም ነው ያስገነዘቡት።
አቶ ሽፈራው ሰሎሞን የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ የመግባቢያ ስምምነቱ ዋና አላማ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት የማማከር አገልግሎት በመሆኑ በሀገሪቷ የተመሠረቱ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች በዚህ የማማከር ጥራት ውስጥ ያለፉ በመሆናቸው ዩኒቨርሲቲዎችና የዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎችም በሂደቱ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ እንደነበሩ ተናግረዋል። አክለውም በተለይ የአፕላይድ ዩኒቨርሲቲዎች ተቋማዊ ሆነው የራሳቸውን የገቢ ምንጭ እንዲፈጥሩና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስገድድ የህግ ማእቀፍ ተዘጋጅቷል ብለው የዛሬው MOU ስምምነት ይሄንን ትስስር ለመፍጠር የታሰበ እንደሆነም ተናግረዋል። በተጨማሪም በዋናነት አማካሪ ድርጅቱ ስራዎች ሲኖሩ ላብራቶሪዎችን፣ ወርክሾፖችን፣ የሰው ሀይልና ሌሎች የዩኒቨርሲቲውን ግብአቶች በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ስምምነት እንደሆነም ነው ዋና ስራ አስኪያጁ የተናገሩት። በውጭ ያለው ተሞክሮ የሚያሳየው ሀገርን፣ ከተማንና ትውልድን እየቀየሩ ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች በመሆናቸው በእኛም ሀገር ለአፕላይድ ዩኒቨርሲቲዎች የተሰጠው ትኩረት መሬት ወርዶ ውጤት እንዲያመጣ አማካሪ ድርጅቱ የማማከር ስራዎችን በመስራትና ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ወደ ስራ በማስገባት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።



Leave a Reply